እንኳን ወደ ቅዱስ ባስልዮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በደህና መጡ! በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ስም የተሰየመው የዚህ ኮሌጅ ኃላፊ ሆኖ ማገልገል ክብርም መታደልም ነው። የኮሌጁን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት ዘወትር በመምራት እንተጋለን። ኮሌጁ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮት ጥልቅ ዕውቀትን ለማዳረስና የምእመናንን ሕይወት በእምነት፣ በዕውቀት፣ በመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለመቅረጽ ከተቋቋሙት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
የደብረ ብርሃን ቅዱስ ባስልዮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎቻችን የዘመናዊውን ዓለም ውስብስብነት ለመከታተል የሚረዱ መንፈሳዊና ዘመናዊ ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ ጊዜ የማይሽረው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና አስተምህሮን ለመስጠት ዛሬም እንደ ትላንቱ በትጋት ለመሥራት ተዘጋጅተናል፡፡ ኮሌጁ በነገረ መለኮት፣ በሕግ፣ በቱሪዝምና ቅርስ አስተዳደር የትምህርት ዘርፎች ላይ የአካዳሚክ የልሕቀት ማእከል ለማድርግ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችንን ልጆች በእምነት፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሕይወት የሚበለጽጉበት መካነ አእምሮ እንዲሆን ጭምር ነው። በኮሌጁ የሚሰጠው ሁለገብ ትምህርት መንፈሳዊ ጉዞን የሚያሳካ የጥበብ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ዕውቀት አድማስን ለማስፋት የሚጠቅም ነው፡፡
የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞቻችን እያንዳንዱን የመማር ማስተማር ሂደት ለመደገፍ ለማጠንከር ቁርጠኛ ናቸው። በአንድነት በትምህርት የላቀ ደረጃን እየተቀበልን የእምነታችንን እሴቶች ለመጠበቅ እንጥራለን። በኮሌጃችን ትምህርት ጉዞ ውስጥ በምትገቡበት ጊዜ የሚጠብቃችሁን የመማር፣ የመመራመርና የአገልግሎት እድሎች እንድትጠቀሙ እናበረታታችኋለን። የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮዋን በማስከበር የቆየ ትውፊቷን ትጠብቁ ዘንድ አደራችን የጠበቀ ነው፡፡ በቅዱስ ባስልዮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቆይታችሁ እምነታችሁን በማጠናከር፣ ግንዛቤያችሁን በማስፋት፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለኅብረተሰቡ ትርጉም ያለው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ እንደምታደርጉ የፀና እምነት አለን። በመጨረሻም የኮሌጁ ማኅበረሰብ አካል ለመሆን ስለመረጣችሁ እናመሰግናለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አባ ቀሌምንጦስ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በመ/ፓ/ጠ/ጽ/ት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ባስልዮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ